ኢባትሎአድ ለሞጆ ከተማ አስተዳደር ባደረገው ድጋፍ የተሰራ የቴክኒክ ወርክ-ሾፕ ተመረቀ

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ለሞጆ ከተማ አስተዳደር ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ የተሰሩ ሁለት የቴክኒክ ወርክ-ሾፖች የኢባትሎአድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ እና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ሰኔ 09 ቀን 2012 ዓ.ም ተመርቀዋል፡፡ የሞጆ ወጣቶች የቴክኒክ ወርክ-ሾፖች ስራ 5.7 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው ሲሆን ይህም ኢባትሎአድ ለሞጆ ከተማ አስተዳደር ከ35.9 ሚሊዮን በላይ ብር መድቦ የሚያከናውነው የልማት ፕሮጀክት አካል ነው፡፡ ኢባትሎአድ የተጣለበትን ታላቅ ሃገራዊ ሃላፊነት ከመወጣት ባለፈ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍም ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ሲሆን በተለይ በሞጆ ከተማ ውስጥ ያለው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን ለከተማ አስተዳደሩ ያለውን አጋርነት ለማሳየት ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የተለያዩ የልማት ስራዎች እያከናወነ ይገኛል፡፡ ኢባትሎአድ በሞጆ ከተማ ካከናወናቸው የልማት ስራዎች መካከል የአረንጓዴ ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃና ፅዳት፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ የቴክኒክና ሙያ ወርክሾፕ ስራዎች እና የሞጆ ስፖርት ክለብን የማጠናከር ስራዎች ለአብነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡