ጊቤ መርከብ በርበራ ወደብ ገባች

ድርጅታችን ወደ በርበራ ወደብ መደበኛ አገልግሎት (regular scheduled liner service) መስጠት የጀመርንበት የመጀመሪያውን ታሪካዊ ጉዞ ግቤ በተባለችው የኢትዮጵያ መርከብ ማሳካት የቻልን መሆኑን በደስታ እንገልፃለን። በዚህ መልኩ አንድ ተብሎ በግቤ የተጀመረው አገልግሎት የሚቀጥል ሲሆን ሸበሌ የተባለችው መርከባችን ደግሞ ከሣምንት በኋላ በርበራ ወደብ ትደርሳለች። የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት መርከብ የሆነችው የግቤ መርከብ ወደ ስፍራው ስትገባ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ፣ በሱማሊያ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል ሰኢድ ሙሃመድ ጅብሪል እና ሌሎች የሚመለከታቸው የDP World Berbera የወደብ አስተዳደር ሃላፊዎች በቦታው ተገኝተው የስራ ሂደቱን በመጎብኘት ደማቅ አቀባበል አድርገዋል። ጊቤ እና ሸበሌ መርከቦቻችን በገልፍ ኢንድያ ሰብ ኮንትነት ውስጥ ባለው መስመር እቃን የማጓጓዝ ስምሪት ተሰጥቷቸው የሚሰሩ ሲሆን ወደ በርበራ ወደብ የተጀመረው አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቅጥል በማድረግ የድርጅታችንን አገልግሎት ሽፋን ለማስፋትና ለማሳደግ የያዝነው ዕቅድ አንድ አካል ሲሆን፤ በተጨማሪም የበርበራ-ኢትዮጵያ ኮሪደር ለአገራችን ገቢና ወጪ ንግድ ተወዳዳሪ አገልግሎት የሚሰጥበትን ቀጣይ ሥራ መሠረት ከማስቀመጥ አንፃር ከፍትኛ አስትዋፅዖ እንደሚኖረው ታይቷል፡፡ ጊቤ መርከብ በአሁኑ ጉዞዋ አስራ አንድ ሺ ሁለት መቶ ቶን የፍጆታ ዕቃ ይዛ ለሶማሌላንድ ገበያ ማጓጓዟ የተገለፀ ሲሆን በቀጣይም ተመሳሳይ መጠን ጭና ከምትመጣው ሸበሌ መርከብ ጋር የሚሰራው ስራ ከዚህ በፊት ድርጅቱ በስፍራው ከሰራቸው ስራዎች በእጥፍ እንደሚበልጥና በቀጣይም እድገቱ እየጨመረ እንደሚሄድ ተገልፃል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በወደቡ ላይ የተሰማሩ በርካታ ባለ ሃብቶችና ሃገራት ከፍተኛ የማልማትና የመገልገል ጥያቄ ማቅረባቸውና የስራ ፍላጎት ማሳየታቸው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የወደቡ ዓለማቀፋዊ ተቀባይነትና አመቺነት ነው። በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት ታሪክ የአገራችን መርከቦች ወድ በርበራ ወደብ ጉዞ ሲያደርጉ ከሃያ ዓመት በኋላ የጊቤ መርከብ የመጀመሪያዋ ሆናለች።