ኢባትሎ የሎጅስቲክስ ዘርፉን የሚያዘምኑ 100 አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን አስመረቀ

ኢባትሎ የሎጅስቲክስ ዘርፉን የሚያዘምኑ 100 አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን አስመረቀ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የሀገሪቱን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አቅም ይበልጥ ለማሳደግና ቀልጣፋ አገልግሎትን ለማረጋገጥ ግዙፍ ኢንቨስትመንት ያረፈባቸውን 100 አዳዲስ ተሽከርካሪዎች በዛሬው ዕለት በይፋ ስራ አስጀምሯል። የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ብሩክ ታዬ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ምሰሶ ተሸክመው ሌት ተቀን ለሚሰሩ አሽከርካሪዎች የላቀ ምስጋና አቅርበው፣ የኢትዮጵያን ስም በድንበር ተሻጋሪ መንገዶች ላይ ከፍ ያደረጉ የኢኮኖሚያችን ጀግኖች መሆናቸውን በማንሳት፣አሽከርካሪዎች በሀገር ፍቅርና በሙያ ስነ-ምግባር ተግተው ስራቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል። የኢባትሎ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አብዱልበር ሸምሱ በበኩላቸው፣ እነዚህ 100 አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ድርጅቱ ቀደም ሲል ካሉት 556 ተሽከርካሪዎች ጋር ተዳምረው የሎጅስቲክስ ስራን በከፍተኛ ሁኔታ ለማዘመን እንዲሁም ለማቀላጠፍ፣ የተሽከርካሪ እጥረትን በዘላቂነት ለመቅረፍ ድርጅቱ በሚደርስባቸው 345 ዓለም አቀፍ የወደብ መዳረሻዎች የሚንቀሳቀሰውን የጭነት ፍሰት ለማሳለጥና እያደገ የመጣውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው ገልፀዋል። የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ድርጅቱ ለሀገሪቱ ወጪና ገቢ ንግድ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ አድንቀው፣ አስተዳደራቸው ለተቋሙ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። በመርሃ-ግብሩ ማጠቃለያ ላይ ተሽከርካሪዎቹን ለአገልግሎት ብቁ በማድረግ ረገድ በቴክኒክና በጥገና ስራ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ የድርጅቱ ሰራተኞች የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።