ኢባትሎአድ በዓለም ባንክ የብድር ድጋፍ የተገዙ አዳዲስ የወደብ ማሽነሪዎችን ርክክብ ፈጸመ

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር በማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን በመተግበር ላይ ባለው የሞጆ አረንጓዴ ሎጅስቲክስ ማዕከል ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር 49 አዳዲስ የወደብ ማሽነሪዎችን ጥር 27 2013 ዓ.ም. የትራንስፖርት ሚኒስትር እና ዲኤታዎች፣ባለድርሻ አካላት፣ተባባሪዎች እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ከማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ርክክብ ፈጸመ፡፡ በዕለቱ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ ለዝግጅቱ ታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የኢባትሎአድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ በዓለም ባንክ የብድር ፋይናንስ የሚተገበረው የሞጆ አረንጓዴ የሎጅስቲክስ ማዕከል ፕሮጀክት በቀጣይ በገቢና ወጪ ንግዱ ላይ በሎጅስቲክሱ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው ቢሆንም በተፈለገው ጊዜ እና ፍጥነት ከማጠናቀቅ እና ወደ ስራ ከመግባት አኳያ ሲመዘን ፕሮጀክቱ መጓተት የሚታይበት በመሆኑ የፕሮጀክቱ አመራር ላይ አስፈላው ድጋፍና ክትትል በማድረግ የፕሮጀክት ትግበራው ተገምግሞ ፕሮጀክቱ የዘገየበትን ጊዜ በሚያካክስ ፍጥነት እንዲጠናቀቅ በትህትና ጠይቀዋል፡፡ ማሽነሪዎቹ 19.6 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ተደርጎባቸው በበድር የተገዙ ሲሆን የዕዳ ክፍያው ለሃያ ዓመት የተራዘመና አነስተኛ ወለድ የሚታሰብበት በመሆኑ ድርጅታቸው የሚጠበቅበትን ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን በማረጋገጥ ማሽነሪዎቹ ለታለመላቸው አገልግሎት እንዲውሉ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ኦፕሬሽን እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ለሞጆ አረንጓዴ የሎጅስቲክስ ማዕከል ፕሮጀክት ግንባታ የሚያስፈልገውን የመሬት ይዞታ ከማዘጋጀት አንስቶ ሌሎች የሚጠበቅባቸውን ትብብር እንዲያደርጉ ባለድርሻ አካላትን ጠይቀዋል፡፡