ለድርጅቱ የመርከብ ሰራተኞች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተደረገ

በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ለመርከብ ሰራተኞች የኮሮና ቫይረስ የናሙና ምርመራ መደረግ ጀመረ። የናሙና ምርመራ የተደረገላቸው የመርከብ ሰራተኞች ያለፉትን ሶስት ወራት በእረፍት ላይ የነበሩ ሲሆን ይህ ምርመራ እረፍታቸውን በማጠናቀቅ በቀጣይ ወደ ስራ ለመሰማራት የሚያስችል የቅድመ ጥንቃቄ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ምርመራው ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት ጋር በመተባበር በድርጅቱ ዋ/መ/ቤት የተካሄደ ሲሆን በዚህ ወቅት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ተገኝተው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በስራ ቦታ ላይ መወሰድ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ምክር ለግሰዋል፡፡ የመርከብ ሰራተኞች የአገራችንን የወጪና ገቢ ዕቃዎች ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ወደቦች በባህር የሚያጓጉዙ እንደመሆናቸው ዕቃዎችን ከወደብ ሲጭኑም ሆነ ሲያራግፉ ራሳቸውን ከወረርሽኙ መጠበቅ እንዳለባቸውና የተጣለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት ከምንጊዜውም በላይ በብቃት እንዲወጡ ከአደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በድርጅቱ መርከቦች ላይ እየሰሩ የሚገኙ ባህረኞች በየመዳረሻ ወደቦች እንዳይወርዱ እንደሚደረግና ዕቃ ከወደብ የመጫንና የማራገፍ ሥራው በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተሰራ እንደሚገኝ ካፒቴን ተፈራ በዳሳ የሽፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስረድተዋል፡፡ የመርከብ ሰራተኞች ወደ ጅቡቲ ሲጓዙ ድርጅቱ ባዘጋጀው የየብስ ትራንስፖርት የሚጠቀሙ ሲሆን በጉዞ ሂደት ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ በቀጥታ መርከብ ላይ የሚወጡ ይሆናል፡፡ በጉዞ ሂደት ራሳቸውን እንዲጠብቁ የሚያገለግል የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር እና የፊት መሸፈኛ ማስክ ተሰጥቷቸዋል፡፡