የቃሊቲ የየብስ ትራንስፖርት ቅ/ጽ/ቤት የካይዘን ትግበራ አፈጻጸም ተሞክሮ ለውድድር ቀረበ

በኢትዮጵያ የካይዘን ኢንስቲትዩት አማካኝነት በአገር አቀፍ ደረጃ የተሻለ የካይዘን አፈጻጸም ያላቸውን ተቋማት ለመለየት በሚያስችል ውድድር ላይ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የቃሊቲ የየብስ ትራንስፖርት ቅ/ጽ/ቤት የካይዘን ትግበራ አፈጻጸም ተሞክሮውን አቀረበ፡፡ በቪዲዮ ኮንፈረንስ በተደረገው በዚህ ውድድር ላይ ኢባትሎአድን ጨምሮ ከዘጠኝ በላይ አገር አቀፍ ተቋማት ተሞክሯቸውን አቅርበዋል፡፡ ዓላማውም እ.ኤ.አ መስከረም ወር 2020 ላይ በቱንዚያ ለሚካሄደው የአፍሪካ ካይዘን ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ የተሻለ የካይዘን አተገባበር ያላቸውን ተቋማት ለመለየት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ እንደሚታወቀው በቃሊቲ የየብስ ትራንስፖርት ቅ/ጽ/ቤት የካይዘን ፍልስፍና አተገባበር የጀመረው ባለፈው ዓመት ቢሆንም በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ስራዎች ተሰርተው አመርቂ ውጤቶች መመዝገብ ችለዋል፡፡