በድርጅቱ በያዝነው የክረምት ወቅት ከ22 ሽ በላይ ችግኞች ተተከሉ

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የዋናው መ/ቤት እና ቅ/ጽ/ቤት አመራሮች እና ሰራተኞች እስካሁን ድረስ ከ22 ሽ በላይ ችግኞችን ተክለዋል፡፡ የችግኝ ተከላ የተካሄደው በቅርንጫፍ መ/ቤቶች እና ሞጆ ወደብና ተርሚናል አቅራቢያ በሚገኘው ከሎሜ ወረዳ በተሰጠ 17 ሄክታር መሬት የድርጅቱ ጥብቅ ደን ላይ ሲሆን ችግኞችን በመትከል የተራቆተ መሬትን በደን በመሸፈን ሀገራችን እየተገበረች ያለውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጅ መደገፍ የሚያስችል ዓላማ እንዳለው ተገልጿል፡፡ ድርጅቱ በተረከበው ቦታ ላይ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ የተለያዩ የፍራፍሬ እና አገር በቀል ችግኞችን መትከል የተቻለ ሲሆን ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ እንዲጠበቅ አጥር በማጠር፣ የአካባቢው ወጣቶችን በማደራጀት ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና ችግኞችን እንዲንከባከቡ በማስቻል እንዲሁም ቦታው ከለማ በኋላ ለወጣቶች በቋሚነት የገቢ ማስገኛ እንዲሆን ለማድረግ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ድርጅቱ በዚህ የክረምት ወራት በተደረገው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ከዋናው መ/ቤት በተጨማሪ በቃሊቲ፣ ሞጆ፣ ገላን፣ ባቦጋያ፣ ወረታ፣ መቀሌ እና ድሬዳዋ ቅርንጫፍ መ/ቤቶች 22,420 ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት 23 ሽ ችግኞች መተከላቸው የሚታወስ ሲሆን በአጠቃላይ ከ45 ሽ በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡