በድርጅቱ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተጀመረ

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ በድርጅቱ የሚከናወነውን የ2012 የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አስጀመሩ፡፡ የችግኝ ተከላው የተካሄደው ድርጅቱ በባለፈው ዓመት ከሎሜ ወረዳ በተረከበው 14 ሄክታር ጥብቅ የደን ቦታ ላይ ሲሆን የተራቆተ መሬትን በደን በመሸፈን ሀገራችን እየተገበረች ያለውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጅ መደገፍ የሚያስችል ዓላማ እንዳለው ተገልጿል፡፡ በባለፈው ዓመት በሞጆ ወደብና ተርሚናል ቅጥር ግቢና በጥብቅ የደን ቦታው ላይ ከተተከሉት ችግኞች ውስጥም 90% ያህሉ መጽደቃቸውንና በዚህ የክረምት ወራት ደግሞ 20 ሽ ተጨማሪ ችግኞችን ለመትከል ቅድመ ዝግጅት ተጠናቅቋል፡፡ በባለፈው ዓመት የተተከሉ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ከሰውና ከእንሰሳት ንክኪ ነጻ እንዲሆኑ አጥር በማጠር፣ 30 ለሚሆኑ የአካባቢው ስራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀትና ችግኞችን እንዲንከባከቡ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና ቦታው ከለማ በኋላ ለወጣቶች በቋሚነት የገቢ ማስገኛ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ የክረምት ወራት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ አገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በድርጅቱ ሁሉም ቅርንጫፍ መ/ቤቶች እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡