የኢባትሎአድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ የበጀት ዓመቱን የ9 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም አመልክቶ ዛሬ ግንቦት 27 ቀን 2012 ዓ.ም ለተመረጡ ሚዲያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የ9 ወራት አፈፃፀም የዕቅዱን 102.4% ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ የ2012 በጀት ዓመት የ9 ወራት አጠቃላይ የገቢ ጭነት ነዳጅን (ፈሳሽ ጭነት) ጨምሮ 12 ሚሊዮን ቶን ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ37 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን በመግለጫው ተገልጿል፡፡ በ9 ወራት ውስጥ በአጠቃላይ በሀገር ደረጃ 5.4 ሚሊዮን ቶን ጥቅል እቃ በድርጅቱ የተጓጓዘ መሆኑን የገለጹት አቶ ሮባ አጠቃላይ ብትን ጭነት ደግሞ ማለትም ስንዴ፣ የአፈር ማዳበሪያና የድንጋይ ከሰል ጨምሮ 3 ሚሊዮን ቶን ሲሆን ከዚህ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው በተመሳሳይ በድርጅቱ በኩል የተጓጓዘ ነው ብለዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ 9 ወራት በሁሉም አይነት የድርጅቱ አገልግሎቶች አጠቃላይ 8.55 ሚሊዮን ቶን ዕቃ ማስተናገድ የተቻለ ሲሆን የተሸከርካሪ ጭነት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፃር ቅናሽ ማሳየቱ ተገልጿል፡፡ በሁሉም የኦፕሬሽን ስራዎች ላይ የዕቅዱን 102.4% አፈፃፀም ማስመዝገብ የተቻለ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ4.9 ሚሊዮን ቶን (73%) ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በዋናነት ለጭማሪው ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው ለመጀመሪያ ጊዜ በድርጅቱ በመጓጓዝ ላይ የሚገኘው የአፈር ማዳበሪያ እና የስንዴ ጭነት እንደሆነ አቶ ሮባ ገልጸዋል፡፡ ኢባትሎአድ በበጀት ዓመቱ 1.45 ሚሊዮን ቶን የአፈር ማዳበሪያን ከመነሻ ወደብ እስከ አርሶአደሩ ድረስ የማድረስ ስራን ሙሉ በሙሉ ወስዶ እየሰራ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 1.3 ሚሊዮን ቶን ጅቡቲ ወደብ መድረሱን የተናገሩት አቶ ሮባ ወደብ ከደረሰው ውስጥ ደግሞ 10 ሚሊዮን 7መቶ ሺ ኩንታል ወይም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን እና አፈፃፀሙ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ስንዴን በባሕር የሟጓጓዝ ስራ ተጠናቆ ሁሉንም ወደብ በማድረስ አስረክበናል ያሉ ሲሆን አፈፃፀሙም አጥጋቢ ነው ብለዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬ በሚፈለግበት ጊዜ እና መጠን ማግኘት አለመቻሉ በበጀት ዓመቱ ያጋጠመ ተግዳሮት መሆኑን የገለጹት አቶ ሮባ ይህም ዕቃዎችን ከወደብ በወቅቱ ለማንሳት እንዳንችል አድርጎናል ያሉ ሲሆን ሌላኛው ተግዳሮት በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ንግድ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረው የኮሮና ወረርሽን ነው ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ ድርጅቱ ከሚሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶች በ9 ወራት ውስጥ 19.4 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት የቻለ ሲሆን ከታክስ በፊት 1.8 ቢሊዮን በላይ ብር ትርፍ በማግኘት የዕቅዱን 103% ማሳካት ችሏል፡፡