በሞጆ ወደብና ተርሚናል ቅ/ጽ/ቤት የኮሮና ቫይረስን (COVID 19) ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያስችል የኬሚካል ርጭት አካሄደ

በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በሞጆ ወደብና ተርሚናል የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያስችል በርካታ ሥራዎች እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ ደረጃ ሚደቅሳ የሞጆ ወደብና ተርሚናል ቅ/ጽ/ቤት ዳይሬክተር ገልጸዋል፡፡ እንደሚታወቀው የሞጆ ወደብና ተርሚናል አብዛኛውን የአገራችንን የወጪና ገቢ ዕቃዎች የሚያስተናግድ እንደመሆኑ መጠን ድንበር አቋራጭ የከባድ ተሽከርካሪ ሹፌሮች፣ አስመጭና ላኪዎች፣ የዕቃ አስተላላፊ ትራንዚተሮች፣ የድርጅቱ እና የሌሎች ተቋማት ሰራተኞች የሚገኙበት በመሆኑ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በወደብና ተርሚናሉ ለሚገኙ ሰራተኞች ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት የመስጠት፣ ማንኛውም ሰራተኛ ሆነ ደንበኛ ወደ ወደቡ ሲገባ የሰውነት ሙቀት እንዲለካ የማድረግ፣ የንጽህና መጠበቂያ ሳሙናና ውሃ በማቅረብ እጃቸውን በሚገባ እንዲታጠቡ የማድረግ፣ ሳኒታይዘር እንዲሁም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (Mask) ለሰራተኞች በማቅረብ ራሳቸውን ከበሽታው እንዲጠብቁ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሰው የሚበዛባቸውን ዋና ዋና የወደቡ አካባቢዎች በመለየት እንደ የመግቢያ በርና ቁጥጥር፣ ቢሮዎች፣ መጋዘኖች፣ ካፌ እና ጋራዥ አካባቢ ያሉትን የጸረ ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት ተካሂዷል፡፡ በተመሳሳይ ቅ/ጽ/ቤቱ ድጋፍ በማድረግ በሞጆ ከተማ በሚገኙ ዋና ዋና መንገዶች የኬሚካል ርጭት እንደተደረገ አቶ ደረጀ አስረድተዋል፡፡