ለ2012/13 የግብርና ወቅት ወደ 1.5ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ የአፈር ማዳበሪያ ላጓጓዙ አካላት የዕውቅና እና የምስጋና ስነ-ስርዓት ተካሄደ

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለ2012/13 የአገሪቱ የምርት ወቅት የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ ላጓጓዙ አካላት ያዘጋጀው የዕውቅና እና የምስጋና የማቅረብ ስነ-ስርኣት ሚኒስትሮች፣የውጭ አገር አምባሳደሮች ከየክልል መንግስታት ቢሮዎች የመጡ ኃላፊዎች፣ባለድርሻ አካላት እና ተባባሪዎች በተገኙበት ጥቅምት 5 ቀን 2013 ዓ.ም እንጦጦ ፓርክ በሚገኘው ኩሪፍቱ ሆቴል በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል፡፡ በዚህ ወቅት ከተገኙት የክብር እንግዶች ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ክቡር አቶ ኡመር ሁሴን የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ክቡር አቶ አወል ዑውግሪስ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ፣ ክቡር አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በጅቡቲ ሪፖብሊክ የኢትጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እና ልዩ መልዕክተኛ ሚስተር አቡበከር ኦመር ሃዲ የጅቡቲ ወደቦችና ፍሪ ዞኖች ባለስልጣን ሊቀመንበር ተገኝተዋል ፡፡ በዕለቱ የኢባትሎአድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለዝግጅቱ ታዳሚዎች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ አቶ ሮባ መገርሳ በንግግራቸው እንደገለጹት ድርጅታቸው በ2012 ብዙ የተሳኩ ክንውኖችን እንዳስመዘገበ የጠቀሱ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ከመነሻ ወደቦች እሰከ ጅቡቲ ወደብ ድረስ 10 ሚሊዮን ኩንታል ብትን የዳቦ ስንዴ በማጓጓዝ ለደንበኞቹ ያስረከበበት፣ 14 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከመነሻ ወደቦች ተረክቦ በ26 ግዙፍ መርከቦች የባህር ትራንስፖርት፣ በ3010 ከባድ የጭነት ተሸከርካሪ ምልልሶች እና 1100 የባቡር ዋገኖች ምልልስ በማጓጓዝ ወደ 103 የአርሶ አደሮች መረከቢያ እና ማሰራጫ መዳረሻዎች ማስረከብ የተቻለበት ውጤታማ ስራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡ ይህ ስራ የተከናወነው በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት የሆነው የኮቪድ ወረርሽኝ በተስፋፋበት ወቅት በመሆኑ የማጓጓዙን ስራ ፈታኝ ያደረገው ቢሆንም ተገቢውን የመከላከያ ስራ በመስራት እና የችግሩ ተጋላጮችን በመደጎም በላቀ ትጋት ስራዎች ሊከናወኑ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ በዕለቱ ዕውቅና የሰጣቸው እና ያመሰገናቸው አካላትም በዚህ ከፍተኛ አገራዊ ኃላፊነት ባለው ተግባር ላይ በመሳተፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ እና ለስራው መሳካት ከፍተኛ ሚና የነበራቸውን አንጋፋ ባለሙያዎች እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ክቡር አቶ ኡመር ሁሴን የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ አወል ዑውግሪስ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር እንዲሁም አቶ መኮንን አበራ የማሪታይም ጉዳች ባለስልጣን በየበኩላቸው ለዝግጅቱ ታዳሚዎች መልዕክት ያተላለፉ ሲሆን የተከበሩ አቡበከር ኦመር ሀዲም በበኩላቸው በጂቡቲና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የጋራ የትራንስፖርት ኮሪደር የማልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚሰሩ እና ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን አጋርነት በመግለጽ የዕለቱን ተሸላሚዎች እና ተመስጋኞች እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡ ከዕለቱ የክብር እንግዶችም የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ይህ ስራ የተሳካ እንዲሆን ከሁሉም በላይ በአስቸጋሪው የኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት እና የአገሪቱ ፈታኝ ወቅት እስከ ገጠር ድረስ በመሄድ ማዳበሪያውን ያጓጓዙ ሹፌሮች ሊሆኑ እንደሚገባ እና በቀጣይም ከዘንድሮው በላቀ ሁኔታ የ2 ሚሊዮን ኩንታል ጭማሪ የሚኖረው የ18 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ የሚጓጓዝ በመሆኑ ከወዲሁ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡ ክቡር አቶ አህመድ ሺዴም በንግግራቸውም መንግስት ለትራንስፖርት ሎጅስቲክስ ብዙ መዋዕለ ንዋይ አፍስሶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነና መስኩ ለሁሉም የአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴዎች መሠረታዊ እንደሆነ ጠቁመው በዘርፉ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እና የአገሪቱን ሜጋ ፕሮጀክቶች እና ሁሉም የልማት ተቋማት ለማገዝ በርትቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አወል ዑውግሪ በበኩላቸው በዚህ ግዙፍ ኦፕሬሽን በሚኒስትሩ ተቋማዊ ክፍሎች የሚገኙ ባለሙያዎች ያደረጉትን አስተዋጽኦ አመስግነው ወደፊት የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት የሚሰሩት ስራ መልካም ውጤት እንደሚያመጣ ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም ፕሮግራሙ አዲሱን የእንጦጦ ፓርክ በመጎብኘት ተጠናቋል፡፡